ህዝበ ሙስሊሙ ለአገሪቱ ሰላም እድገትና አንድነት ተግቶ መጸለይ አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ ግንቦት8/2010 የረመዳን ፆም ህዝበ ሙስሊሙ ለአገሪቱ ሰላም፣ እድገት ብልፅግናና አንድነት ተግቶ የሚጸልይበት ወቅት መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ነገ የሚጀምረውን የረመዳን ፆም በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላ የእስልምና እምነት ተከታዮች ‘የእንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የረመዳን ፆም ለኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት፣  አንድነትና ብልጽግና ተግተን የምንጸልይበት ወር እንዲሆን ተመኝተዋል።

“ጾሙ ወደ ውስጣችን የምንመለከትበት ከራሳችን ጋር ታርቀን ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት ወቅት በመሆኑ ለአገርና ህዝብ የሚበጅ ሀሳብና በተጨባጭ ወደ መሬት የሚወርድ ተግባር እንድንከውንበት እድል ይሰጠናል” ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ህዝቡ በሰላም ተዋዶ በፍቅር ተዋህዶ የመኖር የዘመናት ታሪኩ ዛሬም ነገም ወደ ፊትም አብሮት ይዘልቅ ዘንድ እንደ ሁል ጊዜው በጸሎቱ እንዲማፀን ጥሪ አቅርበዋል።

የረመዳን ወር የተለየ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከመረዳዳት፣ ከአንድነት፣ ከእዝነት ከመስጠት እና ከሌሎች በርካታ መንፈሳዊ ትሩፋቶች ጋር የተዛመደ ወር ከመሆኑ ጋር ስለሚሰናሰል የረመዳን ታላቅነት እና ይዞልን የሚመጣውም በረከት ብዙ ነው፡፡” ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *