የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ባልታወቁ ሰዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ህይወታቸው አለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አዳአ በርጋ ወረዳ የሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ህይወታቸው አለፈ።

አብረዋቸው የነበሩ ሁለት የፋብሪካው ሰራተኞችም ህይወታቸው ማለፉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ጠቁሟል።

የፀጥታ ሀይሎች በአሁኑ ወቅት አጥፊዎቹን አድኖ ለመያዝ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ህብርተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ኮማንድ ፖስቱ ጠይቋል።

በምእራብ ሸዋ ዞን አዳ በርጋ ወረዳ የሚገኘው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የዛሬ ሶሰት ዓመት ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ የገባው ፋብሪካው በማምረት አቅሙ በሀገሪቱ ትልቁ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *